አመሠራረት

ኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲስኤቢሊቲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ታኅህሣሥ 1998 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፍትሕ ሚኒስቴር ተመዝግቦ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ለትርፍ ያልቆመ፣ ከሃይማኖትም ሆነ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የማይወግን አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆነ የልማት ድርጅት (መያድ) ነው፡፡ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት 57 የሚሆኑ ግለሰቦች በአባልነት ያሉት ሲሆን፣ ከነዚሁ መካከል ተመርጠው የማኅበሩን ሥራ በበላይነት የሚመሩ ሰባት የሥራ አመራር ቦርድ አባላት አሉት:: ከሥራ አመራር ቦርድ አባላቱ አብላጫውን ስፍራ የያዙት ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ናቸው፡፡

ኢሲዲዲ አካታች ልማትን በማራመድ በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በሚከናወኑ የልማት መርሀ ግብሮች ውስጥ አካል ጉዳት እንደ ጉዳይና አካል ጉዳተኞች እንደ ባለቤት እንዲካተቱ ለማድረግ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በቅርበት ይሠራል፡፡


የድርጅቱ ራዕይ

የድርጅታችን ራዕይ አካል ጉዳተኛ ሕፃናት፣ ወጣቶችና ጐልማሶች እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው በፆታም ሆነ በማንኛውም ሁኔታ መድልዎ ሳይደረግባቸው እንደሌሎች ዜጐች መብታቸው ተከብሮ የተለያዩ የጤና፣ የትምህርትና የሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች የሥልጠናና የሥራ ዕድል እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑባት ሁሉን አቀፍ ኢትዮጵያን ማየት ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ሁሉን አቀፍ ማኅበረሰብ ውስጥ አካል ጉዳተኞች ተቀባይነት ያገኛሉ፤ የራሳቸው የሆነ ድምፅ ይኖራቸዋል፤ እንዲሁም በማኅበረሰባቸው ሕይወትና ዕድገት ላይ በንቃት ይሳተፋሉ፡፡


የድርጅቱ ዓላማና ተግባራት

1. ግንዛቤ መፍጠር፦

በልማትና በአካል ጉዳት ዙሪያ ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለመርሀ ግብር ነዳፊዎች፣ ለአስፈፃሚዎች፣ ለተመራማሪዎች እና ለሌሎች ባለደንታዎች እንዲሁም ለመገናኛ ብዙኀን ድህነትንና አካል ጉዳተኞችን በሚመለከት በዌብሳይትና በሌሎች ኤሌትሮኒክ የመረጃ አውታሮች እንዲሁም መጽሔቶችን በመጠቀም መረጃ ማሰባሰብና ማሰራጨት፤

በአካል ጉዳተኞችና በአካል ጉዳት ዙሪያ ጥናትና ምርምር ማካሄድ እንዲሁም ሌሎች የጥናትና የምርምር ተቅዋሞችና ዩኒቨርሲቲዎች በጉዳዩ ላይ ምርምር እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፡፡

2. አካታች ልማትን ማስፋፋትና ማፋጠን፦

ከአካል ጉዳተኞች ማኅበራትና ከልማት ተቅዋማት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ በድህነትና በአካል ጉዳት ጉዳይ እንዲሁም አካል ጉዳትና አካል ጉዳተኞችን በአጥጋቢ ሁኔታ በልማት ፖሊሲና መርሀ ግብር ውስጥ ለማካተት የሚያስችሉ ዘዴዎችን የሚያስጨብጡ ሥልጠናዎችን ለመንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ሠራተኞች ማዘጋጀት፡፡

3. የአቅም ግንባታ ማድረግ፡-

አካል ጉዳተኛች፣ ቤተሰቦቻቸውና ድርጅቶቻቸው ችሎታቸውና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው እንዲጎለብት በማህበረሰቡ ዉስጥ ለሚገኙ የአካል ጉዳተኛ ሰዎች ቡዱኖችና የአካል ጉዳተኛ ልጆች ቤተሰቦች ማህበር ለለጋሽ ድርጅቶች የሚቀርቡ አጫጭር ፕሮጀክቶች እንዴት መቅረፅና ማዘጋጀት እንደሚቻል የቴክኒክ ድጋፍ ይሰጣል የገንዘብ አቅማቸው እንዲጎለብት ማገዝ።

4. የአካል ጉዳተኞችን የትምህርት ዕድል ማሳደግ፦

በከፍተኛ ትምህርት ተቅዋማት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ካሉ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ጋር በመሥራት ተቅዋማቱ በየዓመቱ በሚቀበሉት አጠቃላይ የተማሪዎች ቁጥር ውስጥ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ቁጥር ማብዛትና ወደ ተቅዋማቱ ለሚገቡት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፤

እንደ ሥነ-ትምህርት፣ ኢኮኖሚክስ፣ ሕግና ማኅበራዊ ሳይንስ ባሉ የትምህርት ክፍሎች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ አካል ጉዳትና ልማት አንዱ የምርምር ዘርፍ እንዲሆን ማስቻል፡፡

5. የጥናትና ምርምር ስራዎች ማካሄድና ማስፋፋት፦

በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኛ ልጆች፣ ወጣቶችና ጎልማሶች እንዲሁም የቤተሰቦቻቸው ሁኔታ አስመልክቶ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የምርምር ሥራዎችን ማስፋፋትና ማካሄድ። ይህም ዕድሎችን ለማስፋትና ፍላጎቶችን ለማርካት የተሻሉ አማራጮችን ለመንደፍና ለማፈላለግ በማሰብ ነው።

6. አገልግሎቶችን ማመቻቸት፦

የምልክት ቋንቋ፣ የትርጉም አገልግሎት መስጠት፣ የቀለም ጽሑፎችን ወደ ብሬል መቀየር፣ ለእንቅስቃሴ ምቹ የሆኑ ተሽከርካሪ ወንበሮችና ምቹ የሆኑ የመሰብሰቢያ አዳራሾች እንዲሁም የመገናኛ ብዙኀን ተሳትፎዎች እንዲኖሩ ማድረግ፤

Back