ወደ ኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲስኤቢሊቲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ድረ-ገፅ እንኳን በደህና መጡ!

የኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲስኤቢሊቲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ማኅበር (ኢ. ሲ. ዲ. ዲ.) እንደ እ.ኤ.አ. ታኅሣሥ 2005 በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፍትሕ ሚኒስቴር ተመዝግቦ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ለትርፍ ያልቆመ፣ ከሃይማኖትም ሆነ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የማይወግን አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆነ የልማት ድርጅት (መያድ) ነው፡፡ ኢ.ሲ.ዲ.ዲ. በኢትዮጵያ ከአሥር አንድ እጅ ለሚገመቱ አካል ጉዳተኛ ሕፃናት፣ ወጣቶችና ጎልማሶች እንዲሁም ቤተሰቦቻችው የሚገኙበት የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል ሳይታክት ይሠራል። ይህን ለማስፈፀምም በርካታ የድርጊት መርሃ-ግብሮች በመቅረፅ በአካል-ጉዳተኛ እና ጉዳት-አልባ በሆኑ ጊዚያዊና ቋሚ ሠራተኞች የተገነባ የሰው ኃይል አደራጅቷል።

ኢሲዲዲ አካታች ልማትን በማራመድ በኢትዮጵያ በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በሚከናወኑ የልማት መርሃ-ግብሮች ውስጥ አካል ጉዳት እንደ ዋነኛ ጉዳይና አካል ጉዳተኞች እንደ ባለቤት እንዲካተቱ ለማድረግ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በቅርበት ይሠራል፡፡

ኢ.ሲ.ዲ.ዲ በኢትዮጵያ በአካል ጉዳተኛነት ዙርያ የተለያዩ መረጃዎች በማሰባሰብ በጽ/ቤቱ የመረጃ ማእከል አደራጅቷል፡፡ ይህ የመረጃ ማእከል አካል ጉዳተኝነትን አስመልክቶ የተለያዩ ሰነዶች፣ መፅሃፍትና የኤለክትሪክ መረጃዎች እንዲሁም በአገሪቱ ለሚገኙ አካል ጉዳተኛ ሰዎች ፍላጐት ለማሟላት የተቋቋሙ ድርጅቶችና አገልግሎቶቻቸው ያካተተ ነው፡፡


Back